Democracy: Liberty, Security, & Prosperity

Archive for July, 2010

Interview with Awrambatimes ( A weekly Amharic news paper)

Posted by Jawar on July 27, 2010

June, 2010

awramba_122

ቃለ ምልልሱን ለመጀመር ያህል ስለትውልድህ፣ እድግትህ እንዲሁም ከሀገር የወጣህበትን ወቅትና ምክንያት ብትገልጽለን?

የተወልድኩት የናቴ ዘመዶች በሚኖሩባት አርሲ አሰኮ ውስጥ በምትገኝ ዲማ ተብላ በምትጠራ አከባቢ ነው አሉ። እናቴ ኡልማ እንደወጣች ወደቆላ ተወስኩ። በኋላም  በሃረርጌና አርሲ ድንበር ላይ ባለችው ዱሙጋ በምትባል ትንሽ ከተማ አደኩ። እዚያው ትምህርት ጀምሬ አንደኛ ደረጃን ለማጠናቀቅ ትንሽ ሲቀረኝ በተፈጠረ ችግር ወደ አሰላ ተዛውሬ 8ኛ በአሰላ ሚሽን፣ 9ኛ ደግሞ ጭላሎ ተማርኩ። ከዚያ ወደ አዳማ ሄጄ የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በ1994 ተፈትንኩ፣ 11ኛ እየተማርኩ ሳለሁ የስኮላርሽፕ እድል አግኝቼ በ1995 ወደ ሲንጋፖር ሄድኩ።  በዩናይትድ ዎርልድ ኮሌጅ ኦፍ ሳዉዝ ኢስት ኤዢያ ለሁለት ዓመት ከተማርኩ በኋላ ካሊፎርኒያ ዉስጥ ወደሚገኘው እስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ባለፈው አመት በፖሊቲካል ሳይንስ ተመረኩ። በስታንድፎርድ ቆይታዬ በኦክስፎርድ፣ በህንድ እንዲሁም በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር የማካሄድ እድል ነበረኝ። አሁን ያንኑ ምርምር በግሌ ለመቀጠል ወደ ዋሽንግቶን መጣሁ።

በአሁኑ ሰዓት በበርካታ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ  ፖሊቲካዊ ኮሜተሪዎችን  በድህረገጾችና ብሎጎች ላይ በመፃፍ ትታወቃለህ።ባልሳሳት እንዲህ አይነቱን ተሳትፎ የጀመርከው በቅርቡ ነው። ከሁገር ከመውጣትህ የነበሩ ሁኔታዎችን እንዴት ታስታውሳቸዋለህ?

ትውልዴ፣ አስተዳደጌ እና ትምህርቴ ማሕበራዊና ፖሊቲካዊ ሂደቶችን በቅርብ እንድከታተል እድል ሰተውኛል። ከሁለቱ ዋና ያሀገርችን ሃማኖቶች ከፈለሰ ቤቴሰብ እንደመወለዴ ልዩነትን ማወቅና ማክበርን፤ መቻቻልን ማጎልበትን፣ ግጭቶችን በጥንቃቄ ማስወገድና መፍታትን መልመድ የተወለድኩበት ግዴታ ነበር። ገና ትንሽ ልጅ እያለሁ አከባቢያችን በኦነግ ቁጥጥር ስር ስለ ነበር  ከጠዋቱ ለፖሊቲካዊ አካሄዶችና አመለካከቶች ተጋለጥኩ። ህወሃት እና ሻቢያ አከባቢያችንን በወረሩበት ወቅትም የጦርነትን አስከፊነት፣ ጭካኔንና ጭቆናን በቅርብ ማየት ተገድጄያለሁ። ለትምህርት በተለያዩ የሃገራችን ከፍሎች በመዘዋወሬ ደግሞ የሃገሪቷን ገጽታ በቅርብ ማየትን ችያለሁ።

በውጭ ሁገር የነበረህ ተሞክሮስ እንዴት ነበር? ኢትዮጲያን አስመልክቶ የተለያዩ ማህበራዊ ፖሊትካዊ ዱዳዮችን ብድህረገፆች ላይ ብዝርዝር እንድታነሳ ያስቸለህ ምንድን ነው?

ሲንጋፖር ከሄድኩበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ሃገራትን ጎብኝቻለሁ፣ ከተለያዩ ባህሎች የመጡ ሰዎችን ተዋውቄያለሁ። በዚህ ሂደት ውስጥም የባህል ግጭትን፤ ቋንቋ ችግርን በመወጣት አብሮ መኖርን እራሴን ማስተማር ነበረብኝ። በካናዳ፣ በ አውሮፓና በ ሰሜን አመሪካ የተለያዩ አለም አቀፍ የወጣቶፍ የመራር ስልጥናዎችን ወስጃለሁ፣ በተራዬም ሌሎችን በማሰልጠን ብድር ለመክፈል ሞክሬያልሁ። በማሌዢያ የጎማ ዛፍ ገበሬዎችን አኗኗር አጥንቻለሁ። በ ታይላንድና  የ ተቸገሩ ህጻናትን በሚረዱ ድርጅቶች ውስጥ አግልግያለሁ። በ ላኦስ የ አየር ጸባይ ለውጥ በ ትልቁ የሜኮንግ ወንዝ ዳርቻ ገበረኦውች ልይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት አይቻለሁ። የ ስሪላንካን ጦርነት ለመፍታት የተደረገው ሙከራ አካል የሆነ የወጣቶች ኮንፈረንስን አስተባብሬያለሁ። ወደ አሜሪካ መጥቼ በታወቀ ዩኒቨርሲቲ ግንባር ቀደም በሆኑ ምሁራን ተምሬያለሁ። እነዚህ በህይወቴ ያለፍኩባቸው ሂደቶች በሃገራችን ማህበራዊ፣ ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችና መፍትሄዎች ዙሪያ ሰፋ ያለ የግል ግንዛቤ እንዳጎለብት ረድተዉኛል። ሀገርና ህዝባችንን ወደ ተሻለ የኑሮ ደረጃ ለማድረስ እየተካሄደ ባለው ውይይት ዉስጥ፤ እኔም የራሴን ግንዛቤ ብጨምር ይጠቅም ይሆናል ከሚል ተነስቼ ነው መጻፍ የጀመርኩት።

የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ቦሮሞ ህዝብ ላይ ደረሰ የሚሉትን በደል በመቃወም በተላዩ መንግደች በመታገል ላይ እንዳሉ ይታወቃል።ብውጭ ያሚገኘውን ኦነግን ጨምሮ  ኦፍዴን፣ አህኮ፣ ኦብኮ፣ እንዲሁም ራሱ ኦህዴድንም ጭምር መጥቀስ ይቻላል። የእንዚህን ድርጅቶች ትግል እንዴት ትገመግመዋለህ? ውጤታማነትቸውን እንዴት ትገልጸዋለህ?

የኦሮሞን ህዝብ ትግል በመሪነት ሲያካሂድ የነበረው ኦነግ እየተዳከመ በመሄዱ፣ ባለፉት 20 አመታት ብዙ ድርጅቶች ትግሉን በተሻለ ሁኔታ ለማራመድ ተቋቁመው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። ሆኖም ግን የሚጠበቀባቸውን ውጤት አስገኝተዋል ማለት አይቻልም። ዋነኛው ምክንያት፣ ሁሉም ማለት ይቻላል፣በኦነግ ላይ ባላቸው ንዴትና ተስፋ መቁረጥ ተነሳስተው የተደራጁ ሲሆን፤ ከኦነግ የተለየና የተሻለ ድርጅታዊ ሞዴል፤ ጠንካራ አመራር፤ ውጤት-ተኮር  የትግል ስትራተጂና ታክቲክ ባለመቀየሳችው አልተሳካላቸውም። ስለዚህም  የተሻለ አማራጭ ሆነው የህዝቡን ልብ በመሳብ ከኦነግ ማላቀቀ አልቻሉም። እንደ ኦነግ ነባር፣ ታላቅ ታሪካዊ ሚና ያላዉና ከህዝብ ልብ ዉስጥ የቆየን ድርጅት ለመተካት ቀላል የስምና የፕሮግራም ለውጥ ማድረግ በቂ አይደለም። በስራ በልጦ በመገኘት ብቻ ነው በጭቆና ወላፈን እየተገረፈ ያለን ህዝብ ቀልብ መሳብና ተዓማኒነት ማግኘት  የሚቻለው።

በኦህዴድ በኩል ያለው ችግር ግን ለየት ይላል። ገና ከጠዋቱ የባእድ ተቀጥያ ነው በሚል ኦነግ የከፍተበት ውንጀላና በሂደትም የታየዉ እውነታ ድርጅቱ በህዝቡ ውስጥ ስር እንዳይሰድ፣ ተአማኒነትና ድጋፍ እንዳያገኝ አደረገው። ኦነግ እየተዳከመ ሲሄድ እንኳ እድሉን እንዳይጠቀም የህወሃት ጣልቃ ገብነት ጋሬጣ የሆነብት ይመስለኛል። ይህም የሆነው ኦህዴድ እራሱን የቻለና በህዝብ ተቀባይነት ያለው ድርጅት ከሆነ አፈንግጦ የስልጣን ተቀናቃኝ እንዳይሆን ስለሚፈራ ነው። ይህንን ለመከላከልም አመራሩ፣ አባላቱና ህዙቡ እንዲቆራረጥ ተደርጓል። አመራር ላይ የሚወጡት ግለሰቦች በአባላት የማይወደዱና የማይታመኑ መሆናቸው ተረጋጦ ነው የሚሾሙት። ከተሾሙ በኋላ እንኳን ተወዳጅነትና አማኔታን በስራቸው እንዳይገነቡ ሳይረጋጉ ከቦታቸው ይነሳሉ፤ ወይም ደሞ ተቀናንቃኝ ተፈጥሮላቸው ስማቸው እንዲጠፋና ስራቸው እንዲስተጓጎል ይደረጋል። የክልሉ ፕረዝደንቶች ለአምስተኛ ጊዜ መለዋወጣቸው ነው። ሁሉም ስማቸው ጥፍቶና ታዋርደው ነው የሚለቁት። በዞንና በወረዳ ደረጃ ያሉ አመራሮችማ አንድ ቦታ ላይ ሁለት አመት ሳይቆዩ ነው የሚሽቀነጠሩት። ይህ ደሞ የኦህዴድ መሪዎች ድርጅታዊና ህዝባዊ መሰረት እንዳይገነቡ አግቷቸዋል ። መሰረት የለለው ሰው ደግሞ ሹመት እንጂ ለመምራት የሚያበቃ ስልጣን የለውም። በተጨማሪም ይህ ሁኔታ  ድርጅታዊ አለመረጋጋትና የስራ መመሰቃቀል በማስከተል ውጤታማነትን ያደናቅፋል። ቀድሞውኑ የሚታማ ድርጅት ደግሞ ውጤት አልባ ከሆነ ህዝቡ ውስጥ ሰርጾ የመግባት እድሉ የጠበበ ነው። ለዚህም ነው ምንም እንኳን ብዙ ታታሪ፣ ብልህና ሀገር ወደዳን  ግለሰቦችን ያቀፈ ቢሆንም ኦህዴድ ጭንቅላቱ፣አካላቱና እጎሮቹ እንደተላቀቁ ሰው መራመድ አቅቶት የሚዝለፈለፈው። ከ ሃያ የተደላደለ ጉዞ በኋላ ገና የድርጅትነት መልክ ያልያዘው ኦህዴድ፤እንኳንም የኦሮሞን ህዝብ ሊያገለግል፣  ህልውናውን ማስጠበቅ አልቻለም። ኦነግ ከኢሳያስ እፈርቂ፣ ኦህዴድ ከመለስ ዜናዊ መንጋጋ ራሳቸውን አላቀው በህዝባቸው ጉያ መንቀሳቃስ እስካልቻሉ ድርስ ነጸ አየር ሳየተፍሱ ታፍነው መሞታቸው አይቀሬ ነው።

ከወራት በፊት ከፕሮፈሰር መሳይ ጋር በተከታታይ በድረገጾች ላይ ያደረጋችሁትን ክርክር የተከታተሉ በርካታ ወገኖች ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር ( ኦነግ) አመራሮች አንዱ እንደሆንክ ገምተው ነበር። ለድርጅቱ ያለህ ቅርበት ምን ያህል ነው?

ከላይ እንደጠቀስኩት ለረዥም ጊዜ  ኦነግ ሲንቀሳቀስበት በነበረ አካባቢ ነው ያደኩት። በዚህ ለረጅም ጊዜ በድርጅቱና በህዝቡ መሃከል ከተፈጠረው ቁርኝት በተጨማሪ በነበረው የመንግስት በደል  የተነሳ ኦነግን የማይደግፍ ሰው ነበር ማለት ይከብዳል። እኔም አይኔን የገለጥኩበት ጥርሴን የነቀልኩበት ድርጅት ኦነግ ነው። ተሳትፎዬ ግን በደጋፊነት የተወሰነ ነበር። አባል ሆኜ አላውቅም።

ይህን ማለት የቻልኩበት በተደጋጋሚ ኦንግን የሚመለከቱ፣ እንዲሁም ድርጅቱ እንዴት ጠንካራ ሆኖ መቀጠል እንደሚችልየሚጠቁሙ ጽሁፎችን በማንበቤ ነው።እንዲሁም ይህንን ፅሁፍ የተመለከቱ አንዳንዶች የኦነግን “Blueprint” በአዲስ መልክ እየነደፍክ የገለፅክበት ሁኔታ ነበር።እዚህ ላይ ምን አስተያየት አለህ?

በኦነግ ጥላ ስር ብዙ መስዋእትነት ተከፍሏል። በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ዛሬም በዚሁ ድርጅት ስም ተወንጅለው በየእስርቤቱ ይማቅቃሉ፤ የተቀሩት በየበእድ አገሩ በስደት ይንገላታሉ። ከሃረርጌ ብቻ እንኳን ሰቆቃን ሸሽተው ወደ የመን ሲጓዙ በየወሩ መቶዎች የባህር እራት ይሆናሉ። ይህ በስሙ ህዝባችን የሚሰቃይበት ድርጅት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ፣እየተሽመደመደ ሄዷል።ለዚህ ድክመት ምንጩ መንድነው የሚለው ጥያቄ መልስ ፍለጋ ወደ ሁለት አመት የፈጀ የግል ክትትል እና ጥናት አካሂጃለሁ። በመቶች የሚቆጠሩ ከድርጅቱ የተገለሉና አሁንም ያሉ የጦር አዣጆችን፣ አባላትን፤ደጋፊዎችን፣ የአመራር አባላትንና ውስጥ አዋቂዎችን አነጋገሬያለሁ። እንዲሁም የድርጅቱን ባላንጣና አጋር ቡድኖችን አመለካከትም መርምርያለሁ። የዛን ጥናት ውጤት ነው ጨምቄ ያወጣሁት።ይህንኑ ጽሁፍ ነበር ፕሮፈሰር መሳይ ከበደ እና ሌሎችም የተቹት።

የኦሮሞ ትግል ከተጀመረ ሶስተኛ ትውልድ ላይ ደርሷል። ከግማሽ ምእተአመት በፊት የነበርውን ጭቆና ለመታገል በራያ፣ በባሌና በጨርጨር የተጫረውን አመጽ፣ የዚያን ዘመን አዛውንቶች የመጫና ቱለማን ማህበር በማቋቋም ወደ ሁለገብና አገራዊ ደረጃ አሳደጉት። ምሁሩ ሃ/ማርያም ገመዳ፣ ጀ/ ታደሰ ብሩ፣ ጀ/ ዋቆ ጉቱና ኤሌሞ ቂልጡ የትግሉን መሰረት ጣሉት ማለት ነው። የተማሪዎቹ ንቅናቄ ደግሞ ከነሱ ተረክቦት ኦነግን በመመስረት ትግሉን ወደ ሁለትኛው ምእራፍ አሸጋገረው። በነባራቸው ውስን አቅምም ከፍተኛ ውጤት አስገኝታዋል። ትግሉን ከ ግቡ ለማድረስም የተቻላቸውን ያህል ጥረዋል። አሁን ደሞ ተራው የኛ ነው። እስከ አሁን የተገኙ ውጤቶችን በማስጠባቅ፡ ጉዞውን መቋጨት  ያሁኑ ትውልድ ሃላፊነት ነው። ይህንኑ ሃላፊነት ለመወጣት በአሁኑ ወቅት የጦፈ ውይይት እየተካሔደ ነው። እኔም በዚህ ላይ በመሳተፍ ውይይቱን ለማጎልበት እየሞከርኩ ነው። አብቶቻችን ላደረጉልን ውለታ ልናመስግናቸው እና ልናከብራቸው ይገባል።ሆኖም ግን የግድ የነሱን አሰራርና አመለካከት  ብቻ መከተል አለብን የሚል እምነት የለኝም። እያንዳንዱ የትግል ምእራፍ አዲስ አመለካከት፤ ከዘመኑ ጋር የሚሄድ ስትራተጂና ስልት መቀየስን ይጥይቃል። ፅሁፎቼ በዚህ ዙሪያ ነው የሚያውጠነትኑት።

አምዳምድ ወገኖች ኦነግ ከተመሰረት ጀምሮ ለኦሮሞ ህዝብ ያመጣው ተጨባጭ ለውጥ የለም ይላሉ።እነዚህ ሰዎች ለዚህ መከራከሪያ የሚያቀርቡአቸው ነጥቦች ድርጅቱን ደግፈው የተሰለፉ የተለያዩ የኦሮሞ ተወላጆች በእስር በቶች ሲታጎሩና ሲሰቃዩ አመራሩ ከለላ ከመሆን ይልቅ የታሳሪዎችን ማንነትና ዝርዝር እንኳን አያውቁም።በሆነ ባልሆነው አመራሮቹ ይከፋፈላሉ፣ አንዳንዶቹም በድብቅ መተው ይደራደራሉ ንው። እንደፖሊቲካ ተንታኝነትህ አንተ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለህ?

ኦነግ ከተመሰረተ ጀምሮ ምንም ውጤት አላመጣም የሚለው በጣም የተሳሳተ ግምገማ ነው። ስህተቱም የሚፈጠረው የትግልን ስኬት የምንለካበት መስፈርታችን ትክክል ባለመሆኑ ይመስልኛል። ብዙውን ጊዜ አንድ የፖሊቲካ እንቅስቃሴ ስልጣን እስካልያዘ ድርስ የተሳካለት አይመስለንም። ለምሳሌ የስልሳዎቹ የተማሪዎች (የግራ) ንቅናቄ ምንም ውጤት እንዳላስገኘ ሲፈረጅ እንሰማለን። ግንባር ቀደም የነበሩት የፖሊቲካ  ድርጅቶች ስልጣን ስላልያዙ፣   በአለም ላይ በጥቂት ሃገሮች ብቻ የታየውን የተሳካለት አብዮታዊ ለውጥ ማምጣቱን እንረሳለን። የንቅናቄው ዋና አላማ የነበረው መሬትን ላራሹ መመለስ ሙሉ በሙሉ ተሳክቷል። የብሄርና የሃይማኖት እኩልነት ብዙ ለውጥ ተግኝቷል። ሰፊ ማህበራዊ ለውጦች መጥተዋል። ስለዚህ የተማሪው እንቅስቃሴ አላማ ከሞላ ጎደል ተሳክቷል። እነ ዋለልኝ መኮንን  ስልጣን ቢይዙ ኖሮ ምናልባት እነዚያን ድሎች በማጎልበት የበለጠ ለውጥ ማምጣት ይችሉ ይሆናል። ሆኖም አንድ ፖሊቲካዊ ንቅናቄ ስልጣን ስለያዘ ብቻ የተነሳለትን አላማ ያሳካል ማለት አይቻልም። የኤርትራንና የትግራይን ትግል ብንመለከት ሁለቱም መሪ ድርጅቶች ስልጣን ይዘዋል። ግን ሁለቱ ህዝብ የታገለለትን ዲሞክራሲያዊ ነጻነት፣ የኑሮ መሻሻልና መረጋጋት አገኘ ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው። ኤርትራ ነጻ ወጣች፤ ሆንም ኤርትራውያን የነጻነትን ካባ የተላበሰ ጭቆና፤ ድህነትና ወከባ ነው የቀጠለላቸው። አንድ ልጁን ለትግሉ የሰዋ የትግራይ አዛውንት ያለመውና የተመኘውን ነጻነት፤ ሰላምና ብልጽግና አግኝተሃል ወይ ብትለው መልሱ አሉታዊ ነው። ሃቀኛ የህውሃት ታጋይ እንኳን ድሉ ሚያኮራውም ቢሆንም የድሉ ውጤት ከታገሉለት አላማና ከተከፈልው መስዋትነት አኳያ ሲመዛዘን ተጠቃሚው ስልጣን የተቆናጠጡት ጥቂቶች እንጂ ልጁን የገበረው፤ በረሃብ አለንጋ የረገፈው የትግራይ ህዝብ እንዳልሆነ ይነግረሃል።ስለዚህ ስልጣን መያዝ አንድን ትግል ስኬታማ ያረጉታል ማለት አይቻለም።

ወደ ኦሮሞ ትግል ስንመለስ ሙሉ በሙሉ ተሳክቷል ማለት አንችለም፤ ግን ብዙ አዎንታዊ ለውጦችን ማስገኘቱን አይካድም። የትግሉ ዋና አላማዎች ሶስት ነበሩ። ሀ) የትነጠቀውን መሬት ማስመለስ፣ ለ) ማንነቱን፤ ባህልና ቋንቋውን ማስከበር ሐ) ራሱን ባራሱ ማስተዳደር ነቸው። አሁን ላይ ቆመን ወደኋላ ስንመለከት ትግሉ እንዚህን አላማዎች በአመዛኙ  ማሳካቱን እንረዳለን።  ኦነግም ቢሆን በመጀመሪያዎቹ 15 አመታት የትግል ጉዞው  ከገጠሙት ችግሮች አንጻር አኩሪ ስራዎችን አከናውኗል። ትግሉን ከ አዛውንቶቹ ተረክቦ፤  የህዝቡን ማንነት መልሶ ገንብቶ፣  ወጥ እና ጠንካራ የፖሊቲካ ማህበረሳብ መስርቷል። የህዝቡን ቋንቋ፤ ባህልና ታሪክ በማሳደግ ደረጃ ጉልህ ሚና ተጫውቷል። ይህን ሁሉ ያደረገው ደግሞ ከፍተኛ ድርጅታዊ እንቅፋቶች እያንገዳገዱት ነው።ገና ጫካ በገባ በጥቂት አመታት ውስጥ አብዛኛዎቹ መስራችና ከፍተኛ መሪዎች በድንገት አለቁ። እና ባሮ ቱምሳ፣ አቦማ ምትኩና መገርሳ በሪን የመሳሰሉት መሪዎች ኦነግ ገና በዳዴ መሄድ ሲጀምር ነው የተሰዉት። ስለዚህ  በሁለትኛ ደረጃ ላይ የነበሩት  የመሪነት ሃላፊነት ወደቀባቸው። በኢትዮጵያና ሶማሊያ ጦርነት ወቅት፣ ኦነግ በሁለቱ ሃይሎች መሃከል ተጣብቆ በሁለቱም ሲጠቃ፣ ሁቱንም ሲዋጋ ብዙ የጦር አበጋዞቹን አጣ። ይህን ሁሉ አልፎ ማንሰራራት ሲጀምር ደርግ ወደቀ። ሳይዘጋጅ የ ሽግግሩን መንግስት በተቀላቀለበት ጊዜም ከፍተኛ የስትራተጂ ስተቶች በመፈጸማቸው፣ የድርጅቱን መዋቅር፤ ንብረት፤ ወታደርና የህዝቡን ሞራል ለአደጋ አጋለጠ። ለማንሰራራት የነበሩትን  እድሎችም የባሱ ስህተቶችን በመፈጸም አጨናገፋቸው። የአመራሩ ሃገር ጥሎ መሸሽና ዋና መስሪያ ቤቱን ወደ ኤርትራ መውሰድ ከህዝቡ አቆራረጡት፤ ከትግሉ ሜዳም አራቁት። በቂ አመራር ለመስጠትና ትግሉን ለማራማድ አቃተው። ውጤት አልባነት የአመራር መከፋፈልን አስከትሎ  የባሰ ድርጅቱን አሽመደመዱት። እናም ባለፉት ሃያ አመታት ኦነግ ውጤታማ አልንበረም የሚለው ክስ ትክክል ነው። የመጀሪያዎቹ 15 አመታት ግን አመርቂ ውጤት ያስገኘባቸው ነበሩ። ያለ ኦነግ ግንባር ቀደምነትና ያለ ምሁራኑ ረብርብ ይህ ህዝብ አሁን ያለበት ደረጃ መድረስ መቻሉ ያጠራጥራል። ከንግዲህ ግን ኦነግ እራሱን ለውጦ፣ ችግሮቹን አርሞ ተጠናክሮ ይህን ህዝብ ሊመራ ይችል ይሆን የሚለው አጠያያቂ ነው። የሚያሳዝነው ኦነግ ሙሉ በሙሉ ቢጠፋም በሱ ስም ገዢው ቡድን የ ኦርሞን ህዝብ ማሰቃየቱን አያቆምም።  የ ኦነግን በትንፋሽ መኖር ከ ኦሮሞ ህዝብ ይልቅ አቶ መልስ ዘናዊ የሚፈልገው ይመስለኛል። ባለፉት አስርት አመታት አቶ መንበረጸሃይ የሞትና የ እድሜ ልክ ፍርድ ሲያሸክሟቸው የነበሩት፣ “በደህንነቱ” ታፍነው ጭለማ ከዋጣቸው ሺዎች ውስጥ ከኦነግ ጋር ተጨባጭ ትሥሥር ያላቸው በጣት ነው የሚቆጠሩት።  በኦነግ እያሳበቡ ነገ ህዝቡን ሊመሩ ይሚችሉት ጎበዝ ወጣቶች ያጠፋሉ። ኦህዴድ ውስጥ ጠንከር ያለ ሰው ብቅ ሲል ተፍቆ ኦነግ ይወጣውና ድራሽ አባቱ ይጠፋል። የነገን ሰው ከቀጠፍክበት አንድን ህዝብ አኮላሸህው ማለት ነው። ደግነቱ ይህ ህዝብ ብዙ ነው። አንዱን ሲያጨናግፉት ዘጠኝ ይተካል።

በተለያዩ ወቅት ውጭ ሀገር ሆነው የኦሮሞን ህዝብ ትግል ሲደግፉ ነበር ተብሎ የሚነገርላቸው አንዳንድ ይኪነጥበብ ሰዎች በኦህዴድ አመራሮች ከፍተኛ አቀባብል ተደርጎላቸው ውሎ አዳራቸው ሸረተን ስትመለከት ብግልህ ምን ተሰማህ?

እነዚህ የተከበሩና አንጋፋ ኦሮሞዎች ለረዥም ዘመን ለትግሉና ለማህበረሠቡ  ብዙ ያበርከቱ ናቸው። ወደሃገር የተመለሱት  ከንዴትና ተስፋ ከመቁረጥ  የተነሳ ነው። ከላይ እንደጠቀስኩት ኦነግ ከጊዜ ወድጊዜ እየተዳከመ መሄዱ፤ ብሎም አስቀያሚ የሆነው የውስጥ ሽኩቻቸው ብዙውዎችን አበሳጭቷል። ቅሬታቸውን ሲያሰሙ በካድሬዎች ይዋረዳሉ። አብዛኞቹ ከድርጅቱ ራሳቸውን በማግለል የግል ኖሮ ሲመርጡ አንዳንዶቹ ወደ ሃገር ተመልሳዋል። ገሚሱ ተመላሾች የድርጅቱን አመራር ለማስጠንቀቅ አስበው ይሆናል። ሌሎቹ ደግሞ ህዝቡ በዚህ ድርጅት ላይ ተስፋ ቆርጦ አማራጭ እንዲፈጥር ለማመልከት ይመስላል። ሁሉም ግን ለብዙ ጊዜ በስደት የቆዩ፣ እድሜያቸውም እየገፋ  ከመሆናቸው የተነሳ ተስፋ ለሌለው ድርጅት ብለው ከሚንከራተቱ ይልቅ ሃገራቸውን አይተው ናፍቆትን መወጣት የመረጡ ይመስላል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ለገዥው ቡድን ጥሩ የፕሮፓጋንዳ እድል ፈጥሮለታል። የነዚህን አንጋፋ ሰዎች መመለስ ለ አንድ ሰሞን ከተጠቀመበት በኋላ አዋርዶ መልሷቸዋል። ይህ ደግሞ የተቀረችውን የጡረታ ዘመናቸውን በሰላም ሀገራቸው ለማሳለፍ ማሰብ የጀመሩትን መልሶ ተስፋ አስቆርጧቸዋል።ለነዚህ አዛውንቶች መንከራተት ዋና ተጠያቂዎቹ የኦነግ አመራርና አምባገነናዊው ገዢ ቡድን ነው።

የመድረክ አመራሮች ወደ ሰሜን አሜሪካ በመጡበት ወቅት በተለይ በማሪዮት ሆቴል በተካሄደ ስብሰባ ላይ አንተም ተሳታፊ ነበርክ።በወቅቱ መድረክ በምርጫ ጥሩ ውጤት እንደሚያመጣ አስተያየት ሰጥተህ ነበርና የምርጫውን ውጤት ስትመለክት ምን ተሰማህ?

መድረክ አጀማመሩ ጥሩ ይመስላል። የሃገሪቷን ችግሮች ረጋና ጠለቅ ባለ መልኩ ለመመርመርና አማካይ የትግል አላማ ለመቀየስ ሲያደርጉ የነበረው ጥረት የሚደነቅ ነው። በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ያደረጓቸው ሙከራዎች ጥሩ ነበሩ። ከዚ በመነሳት በምርጫው አመርቂ ውጤት ያመጣሉ የሚል እምነት ነበረኝ። ገዢው ቡድን እንደሚያጭበረብር እርግጠኛ ነበርኩ።  ነገር ግን እንዲህ አይኑን በጨው አጥቦ ለመዝረፍ ያሰበ አልመሰለኝም ነበር። ውጤቱ በጣም ነው ያስደነገጠኝ። ኢህአደግ ምን ያህል እንደተበላሸና ሊቀመንበሩን ስልጣን ምን ያህል ግድ የለሽ እንዳደረጋቸው ስረዳ አዘንኩ። ኢህአዴግ ባለፉት አምስት አመታት ከመጀማሪያዎቹ 15 የተሻለ ስራ በመስራቱ ደጋፊው ባይበዛዊ የሚጠላው ቀንሷል። በተቃዋሚው ጎራ ካለው ቀውስ ጋር ሲደመር ተደላድሉ ማሸነፍ ይችል ነበር። ግን ለህዝቡና አባላቱ ካለው ፍርሃትና ጥርጣሬ፣ በ መሪው እየባሰ የመጣ ማናለኝባት የተነሳ፣እራሱንም ሀገርንም ያዋረደ ውጤት አስታቀፈን።   የ ምርጫው  ውጤት ያም ሆነ ይህ መድረክ ጥሩ ድርጅታዊ መሰረት ጥሎአል። አሁን በደረሰው የምርጫ ውጤት ሳይንደናገጥ ወይም በገኘው  ሞራላዊ ድል ሳይደላደል እራሱን መልሶ ገምግሞ፤ ጥምረቱን አጥናኮር፤ ድርጅታዊ ብቃቱን መንገንባት አለበት። የምርጫው ውጤት ሌሎች ፓርቲዎቻንም ወደ ጥምረቱ ሊያመጣ የሚያስችለው እድል ስልፈጠረለት ሳያታክት ሰርቶ እራሱንን ማስፋት አለበት።

በዚህ ምርጫ ተቃዋሚዎች ውጤት አለማግኘታቸውን አስመልክቶ የተለያዩ ተንታኞፍ የተላያዩ መላምቶችን ያስቀምጣሉ።በአንተ እምነት መስሰረዊ ምክንያቱ ምንድን ነው?

ዋናው መንስኤ ገዢው ቡድን ካለፈው ምርጫ በመማር ጠንካራ ተፎካካሪ እንዳይወጣ የወሰዳቸው እርምጃዎች ናቻው። ይህን አላማ ለማሳካት ሶስት ዋና ዋና ስትራተጂዎችን ተጥቅሟል። 1) ከምርጫው አስቀድሞ ተቃዋሚን ከህዝቡ የመንቀል ስራዎች ተካሂደዋል። የተቃዋሚ ቢሮዎችን በመዝጋት፣ ተመራጮቻቸው ህዝቡን እንዳይጎበኙ በማገድ፣ ስራን እና እርዳታን ለማግኘት የፓርቲ አባልነት ግዴታ እንዲሆን በማድረግ ወዘተ የፓርቲዎች  ድርጅታዊ ተቋም እንዲሽመደመድ አድርጓል። ስለዚህ  በምርጫዎች መካከል  መሰራት የሚገባውን የድርጅታዊ ግንባታ ስራ ተቃዋሚዎች በጠባቧ የምርጫ ዘመቻ ሰሞን ለመስራት መሞከር ተገድደዋል። ይህም አባላትን ማፍራት፣ እጩ ምልመላና ህዝባዊ ቅስቀሳ ሁሉም በአራት ወራት ውስጥ መሰራት ነበረበት።  2) በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ተቃዋሚዎች ጠንካራ እጩዎችና ካድሬዎች እንዳያገኙ ማደናቀፍ። ይህም ለተቃዋሚ ሊሰለፉ የሚችሉ ግለስቦችን በማዋከብ፣ መስፈራራት፤ መደለልና መግደልም ጨምሮ ግለሰቦች ለተቃዋሚ እንዳይወዳደሩ ከፍተኛ ጫና ተደርጓል።የዚህም ማስረጃው ተቃዋሚዎች ተወዳዳሪ ማሳተፍ የቻሉት  80% በታች ለሚሆነው የ ፓርላማ ወበር ብቻ ነው። ለክልሎች ምክርቤት  ደግሞ ከዚያም ያንሳል። ባጠቃላይ ተቃዋሚዎች በቂ እና ብቁ እጩዎችን እንዳያቀርቡ ታግደዋል። 3) በምርጫው እለት የገዢው ፓርቲ አባላት አስመራጭ፣ታዛቢና ድምጽ ቆጣሪ ሆነው የተካሄደ ምርጫ ነበር። በተለይ በገጠሩ። ይህ አላንስ ብሎ አንድ የፓርቲ አባል አምስት ሰው ጠርንፎ ያስመረጠበት ሁኔታ ነበር። ይህ ሁሉ ሲዳበል እንግዲህ ውጤቱ ምን እንደሚመስል ግልጽ። ሆኖም ግን ካርዱ ፈፅሞ ያልተቆጠረ እንደሆን እንጂ በከተሞችና በተወሰኑ ጠንካራ የተቃዋሚ አካባቢዎች ውስጥ ተቃዋሚው ማሸነፍ አይሳነውም ነበር። በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች፤ ምስራቅና መራብ ሸዋ፣ መአራብ አርሲና ምስራቅ ሃረርጌ ተቃዋሚዎች ሙሉ በሙሉ ተሸነፉ ማለት ዘበት ነው።

ለተቃዋሚዎች መዳከም ገዢውን ፓርቲ ብቻ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም የሚሉ ወገኖች አሉ።በዚህ ላይ ያንተ ሀሳብ ምንድነው?

ለተቃዋሚዎች መዳከም የገዢው ፓርቲ አፈና ብቻውን በቂ ምክኒያት ሊሆን ግን አይችልም። 1997 ምርጫ በኋላ በተቃዋሚው ጎራ የነበረው ብጥብጥ፣ ጭቅጭቅና የተወሰዱት እርምጃዎችና ውሳኔዎች ተቃዋሚው ከምርጫው ተጠናክሮ ለመውጣት የነበረውን እድል አጨናገፈው። መሪዎቹ በታሰሩበት ወቅት በውጭ አገር የነበረው ሽኩቻና መሪዎቹ ከተፈቱ በኋል የተፈጠረው መክፋፈል፣ የወሳኝ መሪዎችና ስትራቴጂስቶች ሃገር ጥሎ መሄድ ተደማምሮ የተቃዋሚውን ደጋፊና ህዝቡን አበሳጭቷል። በተቃዋሚ ሃይል ላይ አማኔታ እንዲያጣና ተስፋ እንዲቆርጥ እድርጓል። ለለውጥ ተነሳስቶ የነበረውንም የልብ ትርታ አክስሞታል። በዚህም ምክንያት ዘንድሮ የነበርው የፖሊቲካ አየር ለለውጥ ሃይል የተመቻቸ ነበር ማለት አይቻልም። ስለዚህ በምርጫ 2002 የተወዳደሩት ተቃዋሚዎች ይህንን ሁኔታ የመለወጥ ትልቅ እዳ ነበር የወረሱት። የ ህዝቡን አመኔታ መልሶ መንገንባትና  ተስፋው እንድያቆጠቁጥ ማድረግ ነበረባቸው። ይህ ደግሞ ጠንካራ ድርጅታዊ ብቃት፣ ወጥና ትጉህ አመራር፣ እንዲሁም ከፍ ያለ የገንዘብና የሰው ሃይል ያስፈልገው ነበር። የተወዳደሩት ፓርቲዊችና መሪዎቹ  የተጋፈጡትን አቀበት ለመወጣት  በበቂ ሁኔታ ሰርተዋል ማለት አይቻልም። የተወሰኑት ለውጥ እናመጣለን የሚል የራስ መተማመን ያለቸው አይመስልም። አንዳንዶቹ ደግሞ ጥሩ አላማ ስላነገቡ ብቻ የሚያሸንፉ ይመስላቸዋል። ለውጥ ማምጣት እንደ እርሻ ነው። ለም መሬት ስላለ ብቻ ጥሩ ምርት አይታፈስም። መጀመሪያ ከባዱን የግብርና ስራ እንደምንወጣው በችሎታችን መተማመን አለብን። ከዚያ ዶፉን ተቃቁሞና በሾኅ እይተወጉ ማረስ፣ መዝራት፤ ማረም፤ ወፍ መጠበቅ፣ ማጨድና ወቅቶ ማስገባት ይጠይቃል። ይህን ስራ በኢትዮጲያ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት በበቂ ሁኔታ እየሰራን አይመስለኝም።አንዳንዴ መሬቱን ሳናበስል እንዘራል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዘርተን ሳናርም እንተዋላ። ይባስ ብለንም በ1984 ኦነግ አንዳደርገውና 1997 ቅንጅት እንደደገመው፣  ምርቱን ውድማ ላይ ጥለን ዝናቡን ሽሽት እግሬ አዉጭኝ እንላለን። ይህን አካሄድ ካልቀየርን በኢትዮጲያ ውስጥ ዘላቂና ህዝቡን የሚጠቅም ለውጥ ማምጣት ይቸግረናል።

በምርጫው ማግስት በልጀዚራ ተለቪዥን አስተያየትህን ስትሰጥ ምእራባውያን ከዚህ መንግስት ጋር ያላቸውን ወዳጅነትና እርዳታ የመስጠትን ጉዳይ አንዲያጤኑት ጠይቀሃል።አንዳንዶች ግን ይህ አይነቱ የ “እርዳታ ይከልከል” መከራከሪያ የድሃውን ህዝብ ሁኔታ ያላጤነና ስሜታዊ ሲሉ ይገልጹታል።እርዳታው ሳይቆም ሚሊዮኖች በሚራቡበት፣ እርዳታ መከልከል ከብድ ሰብዓዊ ቀውስ አያመጣም ትላለህ?

እኔ ለ ኢትጵያ የሚሰጠው ሰብዓዊ እርዳታ ይከልከል የሚል ሃሳብ የለኝም። የሰብዓዊ እርዳታው እንደማይቆም አውቃለሁ። ቢቆምም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በማምጣቱ ረገድ ያለው ሚና ውስን ነው። መሆን ያለበት የሚሰጠው እርዳታ በቀጥታ ለተላከለት ችግረኛ ህዝብ መድረሱን ማረጋግጥ ነው። ይህ ደግሞ  የለጋሾቹ ሀላፊነት ነው። ገዢው ፓርቲ የ እርዳታውን እህል ህዝቡን ለማስፈራሪያና ለማስገደጃ እንደሚጠቀም ብዙ መረጃዎች አሉ። ይህ ሙስና ብቻ ሳይሆን ዜጎች ለመብታቸው እንዳይታገሉ፤ ህይወታቸውና ኑሮዓቸው ከ ገዢው ፓርቲ ጋር እንዲቆራኝ ያስገድዳቸዋል።አንድ ፓርቲ ሁሉን የመንግስት አካላት፤ ፍርድቤት፣ ፖሊስ፤ የጸጥታና የመከላከያ ሃይልን በቀጥታ መቆጣጠሩ አንሶ ድሃው የሚቀምስ ያሚልሰውን ከተቆጣጠረው በ ሃገርቱ ፖሊቲካና እኮኖሚ ላይ መጥፎ እንድምታ አለው። ለዚህ ነው ለጋሾች እርዳታን በቀርብ ተከታትለው ችግረኛውን ከችግር የሚያዋጣ እንጂ የሚያብስበት እንዳይሆን መጠንቀቅ አለባቸው ያልኩት። እነዚህ ለጋሾች ኢትዮጲያ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዲያመጥሉን አንጠብቅም። ሆኖም ግን አምባገነንንትን ያሚያባብስ ስራ ከመስራት መቆጠብ አለባቸው።

በመጨረሻ እንደ ማጠቃላያ በሀገር ውስጥ ላሉ ተቃዋሚዎች እንዲሁም ለኢትዮጲያውያን ባጠቃላይ የምታስተላለፈው መልክት ካለ?

በኢትዮጵያ የሀገር ሉአላዊነትን ለማስከበር፣ የዝቦቿን  እኩነትና አንድነት ለማጠንከርና  የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት፣ እውነተኛና ሁሉን አቀፍ ዲሞክራሲያዊ  ሥራዓት ከመገንባት የተሻለ አማራጭ የለም። ላለፉት ገማሽ ምዕት አመታት  ሰላም፣ ፍትህና እኩልነት እንዲነግስ፣ ህዝባችን ከድህነት እንዲላቀቅ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ዜጎች በግልም በቡድንም በመሰላቸው መንገድና አቅጣጫ  ለውጥ ለማምጣት እጅግ ለፍተዋል፤ ከባድ መስዋትነት ከፍለዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ሰፊ መልካም ለውጦች ተገኝተዋል፣ ብዙ ስህተቶችም ተፈጽመዋል። አሁን ባለንበት ጊዜ ላይ ቆመን እነዚህን ያሳለፍናቸውን ሂደቶች በጥሞና መመርመር ይገባል። ጥሩውን ማጎልበት፣ መጥፎውን እንዳይደገም ማስወገድ ይበጃል። እስካሁን ቡድኖች በተናጠል ማምጣት የነበርባቸውንና የሚችሉትን ለውጥ አምጥተዋል። አሁን የተጋፍጥነው የጋራ ችግሮች ናቸው። አንድ ቡድን ብቻውን ቋንቋውን ሊያሳድግ ችሎ ይሆናል፣ የስልጣን ወንደርም ሊቆናጠጥ ይችላል። ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ህብረቀለማት በሆነችና ዘርፈ ብዙ ችግሮች በተጋረጡባት ሃገር አንድ ቡድን ብቻውን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት፤ ዘላቂ ሰላምና የተረጋጋ ማህበራዊ ኑሮ ማምጣት ፈጽሞ አይቻለውም።በተናጠል የምናመጣው ለውጥ ጊዜያዊ እርካታ እንጂ ዘላቂ መረጋጋት አያመጣለንም። ስለዚህ፤ የገራ ችግሮቻችንን አብሮ መፍታት አማራጭ የሌለው በመሆኑ በጽሞናና በዘዴ ወደፊት የምንራመድባቸውን መንገዶች ማቀየስ  አለብን። ይህ ጉዞ ቀላል አይሆንም። ለረጅም ጊዜ የያዝነውን አቋማችንን ማለዛብ ይጠይቃል፣ ከአንድ ወቅት ካስቀየመንና ከበደለን  ጋር ለመስራት እንገደድ ይሆናል። ወኔና ኩራታችንን ማደብዘዝ ይጠይቃል። ይህን መረራ ሂደት በብቃት ከገፋንበት  ኢንደከዚህ በፊቱ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት ወደኋላ የሚያስከድ ለውጥ ሳይሆን  በሶስቱም ወደፊት ልንስፈነጠር እንችላለ። ተስፋ ይኑረን፣ በራስችን እንተማማን፣ ተግተን እንስራ፣ራስችንን እና ሀገርችን መለወጥ እንችላለን።

Advertisements

Posted in Previous Articles | 1 Comment »